News and Social Media Updates

Latest Updates

ኢትዮ ስኳር ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር የስኳር ፋብሪካ ግንባታውን እስኪጀምር ድረስ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በገዛው 10 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ የተለያዩ የግብርና ውጤቶችን በማምረት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በዋናነት እንደ ወንጂና መተሐራ የስኳር ፋብሪካዎችን ከመንግሥት ለመግዛት የተቋቋመው ይህ አክሲዮን ማኅበር፣ ወደ ግብርናውና ተያያዥ ሥራዎች የገባው የስኳር ፋብሪካ ግንባታውን እስኪጀምር አዋጪ በተባሉ ሥራዎች ላይ መሰማራት አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ የአክሲዮን ማኅበሩ አመራሮች ጥር 3 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ የእስካሁኑን እንቅስቃሴና የወደፊት ዕቅዱን በተመለከተ በሰጠው መግለጫ፣ መንግሥት ለሽያጭ ያቀርባቸዋል የተባሉ ስኳር ፋብሪካዎች አሁን ባለው ሁኔታ ለሽያጭ ባለመቅረባቸው በተለያዩ ቢዝነሶች መሳተፍ አዋጭነቱ ስለታመነበት አማራጭ ሥራዎች ውስጥ መግባቱን ጠቁሟል፡፡  

ኢትዮ ስኳር ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር በደቡብ ኢትዮጵያ ኦሞ አሥር ሺሕ ሔክታር መሬትን ከእነ ሙሉ የአግሮ ኢንዱስትሪ ማሽነሪዎችና ግንባታ ጋር አብሮ በመግዛት በቀጥታ ወደ ሥራ መግባቱን ያመለከቱት የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢተው ዓለሙ፣ እርሻውን ከእነ ሙሉ ማሽነሪዎች ከልማት ባንክ የገዙት በ220 ሚሊዮን ብር መሆኑንም አክለዋል፡፡

ከአዲስ አበባ 715 ኪሎ ሜትር አካባቢ ርቀት ያለው የእርሻ ቦታ ቀደም ብሎ በአንድ ቱርካዊ ተያዞ የነበረ ነው፡፡  

ኢትዮ ስኳር ከመነሻው መንግሥት ከሚሸጣቸው ስኳር ፋብሪካዎች መካከል ወንጂና መተሐራ ስኳር ፋብሪካዎችን የመግዛት ዕቅዱ እንደተጠበቀ ሆኖ የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የመጀመርያው ቀዳሚ ዕቅዱን ከወዲሁ ለማሳካት እንዲረዳውም ራሱን እያዘጋጀ እንደሚቆይ የማኅበሩ ቦርድ አባል አቶ እሸቱ ገለቱ ገልጸዋል፡፡

 በመጀመርያው የምርት ዘመን በዓመት እስከ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ስኳር፣ ኢታኖልና 20 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨትን ጨምሮ የተለያዩ የፓራ ሹገር ሥራዎችንና ኤክስፖርት መር ምርቶችን በማምረት የሚቀጥል መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡  

ለስኳር ልማቱ በተለይም ለሸንኮራ አገዳ ተክሉ እርሻ የሚያስፈልገው የማሳ ዝግጅት የተጠናቀቀ መሆኑን ያመለከቱት የአክሲዮን ኩባንያው አመራሮች፣ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡና ከወዲሁ የኩባንያውን የኢኮኖሚ መሠረት የሚያጠናክሩ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የሽግግር ወቅት ምርቶችን የማምረት ሒደት ውስጥ መግባቱንም አስታውቀዋል፡፡  

ዋናው ዓላማ ስኳር ፋብሪካ ገንብቶ ስኳር ማምረት ቢሆንም፣ ሊገዟቸው ተዘጋጅተው የነበሩ የወንጂና መተሐራ ስኳር ፋብሪካዎች ሽያጭ እስኪፈጸም ድረስ በዚህ ሰፊ የእርሻ ሥራ እንደሚከናወንም አስታውሰዋል፡፡

 ፋብሪካዎቹን የመግዛቱ ሒደት ቢዘገይ እንኳን አክሲዮን ማኅበሩ በስኳር ኢንዱስትሪ የካበተ ልምድ ካለው የአውሮፓ ኩባንያ ጋር በአጋርነት ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት በማድረግ በመጀመርያው የምርት ዘመን አንድ ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ለማምረት የሚያስችል አቅም ያለው ፋብሪካ የሚገነባ ሲሆን፣ አሁን ላይ ከፍተኛ ገቢ የሚኝበትን ምርት ለማምረት በመጀመርያው ዙር 570 ሔክታር ላይ ምርቱን ይጀምራል፡፡  

ጎን ለጎን ለስኳር ልማቱ በተለይም ለሸንኮራ አገዳ ተክሉ እርሻ የሚያስፈልገው የማሳ ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑንም ያመለከቱት አመራሮቹ፣ በዚህ የምርት ዘመንም በቅድሚያ የሚያመርታቸውና ለውጭ ገበያ የሚያቀርባቸው ምርቶች የማሾና የሰሊጥ ምርቶች መሆናቸውን፣ ሌሎች ምርቶችንም በተከታታይ እንደሚያመርት አስታውቋል፡፡

በአብዛኛው ለወጪ ንግድ የሚውሉ ምርቶችን የሚያመርት በመሆኑ ከዚህ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪም ለስኳር ፋብሪካ ግንባታ የሚውሉ ማሽነሪዎችን በመግዛት በታቀደው መሠረት የስኳር ፋብሪካውን  ወደ መገንባት የሚገባ ስለመሆኑ አቶ ቢተው ጠቅሰዋል፡፡

የአክሲዮን ማኅበሩን ቀጣይ ተግባራት በተመለከተ አቶ ቢተው እንደገለጹት፣ ኩባንያው በተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች ላይ የሚሠራ ይሆናል፡፡ በተያዘው ዕቅድ መሠረትም በዋናነት ለወጪ ንግድ የሚሆኑ ምርቶችን ከማምረትና ከመላክ ባሻገር በቱሪዝም፣ በሆቴል፣ በነዳጅ ማደያ በአገልግሎትና በሌሎች የቢዝነስ ዘርፎችም ይሰማራል፡፡ በዚህ የሽግግር ወቅት እንደ ስኳር ያሉ ምርቶችንም በማስመጣት ለገበያ ያቀርባል፡፡

 በዚህ የሽግግር ወቅትም ሆነ በኋላ ላይ እንሰማራበታለን ብለው የጠቀሱዋቸው የቢዝነስ ዘርፎች በርካታ በመሆናቸው ይህንን እንዴት ማሳካት ይቻላል? ያላችሁ ፈቃድስ ይህንን ሁሉ ሥራ ለመሥራት ያስችላል ወይ? የሚል ጥያቄ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ እንዲህ ያሉ ሥራዎችን ለብቻቸው የማይሠሩ መሆኑንና በየቢዝነሱ በጋርነት ከሚሠሩ ኩባንያዎች ጋር እንደሚተገብሩ የማኅበሩ ምክትል ሰብሳቢ ኤርሲዶ ላንዲቦ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡   

ብዙዎቹ ቢዝነሶች ከሚገነቡት የስኳር በፋብሪካ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ከመሆናቸውም ሌላ፣ ፋብሪካው ሥራ ሲጀምር ለፋብሪካውም ለአካባቢውም ማኅበረሰብ ጠቀሜታ ያላቸው እንደሚሆን ያመለከቱት ዶ/ር ኤርሲዶ፣ አሁን ባለው ሥራም 100 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥሯል ብለዋል፡፡  

እነዚህ ቢዝነሶች አዋጭ መሆናቸው የሚያመለክተው ማብራሪያ የስኳር ፋብሪካው እስኪገነባ ድረስ የሚያካሄዱት ልማቶችና ቢዝነሶች የሚያስገኙት ገቢ ከፍተኛ በመሆኑ ፋብሪካው እስኪገነባ ድረስ ባለአክሲዮኖች አነስተኛም ቢሆን የትርፍ ድርሻ እንዲያገኙ እንደሚያስችል አቶ ቢተው ጠቅሰዋል፡፡

የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ለማ ጉርሙ በአክሲዮን ማኅበሩ ስለሚገነባው ፋብሪካ እንደገለጹት፣ አንድ ሚሊዮን ኩንታል የማምረት አቅም ያለው የፋብሪካ ግንባታ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥ ዝግጅት ተደርጎበት በአራተኛው ዓመት ላይ የፋብሪካው ማሽነሪ ተከላ ተጠናቅቆ አምስተኛ ዓመት ላይ ማምረት ይጀምራል፡፡ እስከዚያው ግን በኦሞ አካባቢ ኩባንያውን ስም የሚያስጠሩ ትልልቅ ልማቶች ይካሄዳሉ፡፡

የሚገነባው ፋብሪካ ይዘት በአንድ ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቅ እንደሆነም ያመለከቱት ቦርድ ሰብሳቢው፣ የሸንኮራ አገዳ ልማቱም ይህንን የግንባታ ሒደት ተከትሎ የሚከናወን እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡  

እንደ አቶ ቢተው ገለጻ፣ ዋናው የስኳር ፕሮጀክት ወደ ትግበራ ሲገባ ከስኳር ማምረት ሥራው በተጓዳኝነት ወደ 15 የሚሆኑ ምርቶችና አገልግሎቶች ይኖሩታል፡፡ ከእዚህም መካከል ኢታኖል፣ ከረሜላ፣ ችኮሌት፣ ሞላሰስ፣ ኤሌክትሪክ፣ ለሕክምና የሚውል አልኮል፣ የእንስሳት መኖና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

ፕሮጀክቱ ተያያዥ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ለመገንባት የሚያስችል በመሆኑ የስኳር ቱሪዝምና የሎጅ ሆቴል ድጋፍ የባህል ትዕይንት መዝኛዎችንም ለመገንባት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ምርቶችና መሠረተ ልማቶች ኅብረተሰቡን አቀፍ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳ ያላቸው ጉዳዮችን ለማሳካት እንዲቻል ከልማት ባንክ የተገዛው የለማ መሬትና አብሮ የተገዙት በርካታ አግሮ ኢንዱስትሪ ማሽነሪዎች ከፍተኛ ዕገዛ የሚያደርጉ በመሆኑ በቀጥታ ወደ ሥራ እንዲገቡ እንዳስችሉም ከተሰጠው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ በሁለተኛ አማራጭ ይዞ ለመጓዝ የፈለገው መንግሥት ስኳር ፋብሪካዎችን አልሸጥም ወይም ግማሹን እሸጣለሁ በማለቱ ነው ወይ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ አባል ወ/ሮ ረሒማ ሁሴን፣ ‹‹እኛ ወደ ሁለተኛው አማራጭ የገባነው መንግሥት ፋብሪካዎቹን አልሸጥም በማለቱ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

የወንጂና የመተሐራ ስኳር ፋብሪካዎችን ለመግዛት ያለን ዕቅድ አሁንም እንደተጠበቀ ነው ያሉት አቶ ቢተው፣ በማንኛውም ጊዜ መንግሥት ለገበያ በሚያቀርብበት ውቅት ለመግዛት እንሳተፋለን፣ ነገሮች በታቀዱት መጠን እየሄዱ ስላልነበረ መንግሥት እስኪሸጣቸው ድረስ ሁለተኛ አማራጮችን በማፈላለግ በኦሞ ሸለቆ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በገዛነው ሰፊ እርሻና መሣሪያዎች ወደ ሥራ ለመግባት ወስነናል ብለዋል፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ የደቡብ ኢትዮጵያ ኦሞ አካባቢን በ2035 በምሥራቅ አፍሪካ አግሮና የኢኮ ቱሪዝም ኢንዱስትሪና የቱሪዝም ልህቀት ማዕከል ለማድረግ ራዕይ ያለው መሆኑም ተገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት 500 ሚሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታልና ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታል ያለው ሲሆን፣ ተጨማሪ አክሲዮኖችንም በመሸጥ ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡   

FacebookTwitterTelegram

Contact Us

Ethio Sugar Manufacturing S.C

+251116160001
+251116160002
+251116160003
info@ethiosugar.com

Genete Limate Building office no 755/29-3,
Africa Avenue,Woreda 3, Bole sub city,
Addis Ababa,Ethiopia

Copyright © 2024 Ethio Sugar Manufacturing S.C